የዘላቂ ልማት ግቦች የ2017 የፈቃደኝነት ብሔራዊ ግምገማ ተካሄደ

የክልሉ የ2ኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የ2008 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግብ ከታቀደው ያነሰ ቢሆንም ቀጣይ ዕድገት ተመዝግቦበታል

ብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ከክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የዘላቂ ልማት ግቦች የ2017 የፈቃደኝነት ብሔራዊ ግምገማ እና የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የ2008 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መዲና በሀዋሳ ተካሂዷል፡፡

17 ዋና ዋና ግቦችና 169 ዝርዝር ግቦችን ይዞ የተነደፈው የዘላቂ ልማት ግቦች እ.ኤ.አ የ2016 ዓመት አፈጻጸም እንዲገመገም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሃሣብ ሲቀርብ ኢትዮጵያ ለማስገምገም ፈቀደኛ በመሆኗ ይኸው መድረክ በሀገሪቱ 12 ከተሞች የተካሄደ ሲሆን የሀዋሳውም የዚሁ ግምገማ አካል ነው፡፡

አቶ ታምራት ዲላ የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ መድረኩን በንግግር ሲከፍቱ ባስተላለፉት መልዕክት ከሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጋር የተሳሰሩትን የዘላቂ ልማት ግቦች በተሟላ ሁኔታ ከመፈጸም አንፃር ሁሉም ባለድርሻ አካላት በየተሰማሩበት የልማት መስክ ከየሚመለከታቸው የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ጋር የሚመጋገብ የልማት ሥራ ማቀድና ተፈጻሚ ማድረግ እንዲሁም ዕቅዶቻቸውን በጋራ በመገምገም የዘላቂ የልማት ግቦችን አፈጻጸም ማፋጠን ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

አቶ ከበደ ይማም የአካባቢ ደንና የአየር ለውጥ ሚኒስቴር ሚንስትር ደኤታ ስለ መድረኩ ዓላማና አስፈላጊነት ለተሳታፊዎች ባቀረቡት ማብራሪያ የዘላቂ የልማት ግቦች ከዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ያለውን ትስስርና አንድነት እንዲሁም ኢትዮጵያ በዝግጅቱ ወቅት የተጫወተችውን ሚና ከገለጹ በኋላ የ2016 አፈጻጸም ለመገምገም ጥያቄ ሲቀርብ ኢትዮጵያ ለማስገምገም የመጀመሪያ ፈቃደኛ ሀገር በመሆኗ ከ17ቱ ግቦች በስድስቱ ላይ ግምገማው እንደሚካሄድ አስረድተዋል፡፡

ግምገማው የሚካሄድባቸው ስድስቱ ግቦችም:—

  1. ድህነትን ማጥፋት (ግብ 1)
  2. ረሀብን ማጥፋት (ግብ 2)
  3. ጤናማ ህይወትና ደህንነት (ግብ 3)
  4. የሥርዓተ ፆታ ዕኩልነት (ግብ 5)
  5. መሠረተ-ልማት ግንባታና ኢንዱስትሪ ፈጠራ (ግብ 9)
  6. የውሀ ሥነ-ምህዳርን ለዘላቂ ልማት መጠበቅ (ግብ 14)

መሆናቸውን በተጨማሪ ገልጸዋል፡፡

ከብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን እና ከክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ በተወከሉ ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎች በዘላቂ ልማት ግቦች የ2016 አፈጻጸም፣ የኢትዮጵያ እንዲሁም የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የ2008 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡SDG 2017 2

ከሪፖርቶቹ መረዳት እንደተቻለው በ2008 የበጀት ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ ኢኮኖሚው በአማካይ የ8.0 በመቶ ፈጣን ዕድገት አስመዝግቧል፡፡ በበጀት ዓመቱ ግብርና፣ ኢንዱስትሪና አገልግሎት በቅደም ተከተል በ2.3 በመቶ፣ በ20.0 በመቶ እና በ8.7 በመቶ አድገዋል፡፡ እንደ ደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የ2008 በጀት ዓመት ዓመታዊ ዕድገት 6 በመቶ ሲሆን ግብርና እና ተዛማጅ ዘርፎች የ3.2 በመቶ ኢንዱስትሪ የ5.1 በመቶ እና አገልግሎት የ10.3 በመቶ እድገት አሳይተዋል፡፡ በሀገር አቀፍም ሆነ በክልል ደረጃ ለታየው ዝቅተኛ የግብርና ዘርፍ ዕድገት በወቅቱ ኤልኒኖ ያስከተለው የአየር ንብረት ተፅዕኖ እንደሆነ በዋናነት ተጠቅሷል፡፡

በመድረኩ ላይ ሀዋሳ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ የዞኖችና ልዩ ወረዳዎች አስተዳዳሪዎች የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያዎች ኃላፊዎች፣ የሴቶችና ወጣቶች ፌዴሬሽኖችና ሊግ ተወካዮች፣ የህብረት ሥራ ማኅበራት ተጠሪዎች፣ የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች፣ የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮችና የሲቪክ ማኅበራት ተጠሪዎች፣ የሴክተር ቢሮዎች ኃላፊዎች፣ በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ኮሌጆችና ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ተወካዮች በድምሩ 307 ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡