የአሀዳዊ የመጠጥ ውኃ እና የአካባቢ ንጽሕና አጠባበቅ ፕሮግራም (One-WaSH) በጀት አጠቃቀም እጅግ አነስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ

One WaSH

አፈጻጸሙን ለማሻሻል ተቀናጅቶ ለመሥራት የሁሉም ትብብር ተጠየቀ

በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የአሀዳዊ የመጠጥ ውኃ እና የግልና የአካባቢ ንጽሕና አጠባበቅ ፕሮግራም (One-WaSH) በጀት አጠቃቀም እጅግ አነስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡ ቢሮው ይህንን ያስታወቀው ከልዩ ወረዳዎችና ዞኖች ለተውጣጡ የልማት ዕቅድና ኢኮኖሚ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ተጠሪዎችና ለሥነምግባር መከታተያ ኦፊሰሮች ባዘጋጀው ሥልጠና ነው፡፡

አቶ ተፈሪ አያይዘውም የውጭ ሀገር ዜጎች ለሕዝባችን በመቆርቆር ከግብር ከሚያገኙት ብር ቀንሰው ለልማት መለገሳቸው ሳያንስ እነርሱ ተጠቀሙ ብለው የላኩልንን የዕርዳታ ገንዘብ በቀጥታ ለልማት ማዋል አለመቻላችን እጅግ አሳፋሪ ከመሆኑም በላይ በሕዝብ ዘንድ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን የሚያሰነሳ አስከፊ ጥፋት ነው ብለዋል፡፡

በአዲሱ የመጠጥ ውሃ የማዳረስ መርሐ ግብር በገጠር ለአንድ ሰው በ1 ነጥብ 5 ኪ.ሜ ሬዲየስ ውስጥ 20 ሊትር የነበረው አቅርቦት ወደ 40 ማድረስ የተቻለ ሲሆን በከተማ ደግሞ ለአንድ ሰው በዜሮ ነጥብ አምስት ኪ.ሜ ሬዲየስ 40 ሊትር የነበረው ወደ 60 ሊትር ማድረስ የተቻለ ሲሆን ይህንን የዋን ዋሽ ፕሮግራም በጀት አጠቃቀማችንን በማሻሻል ወደላቀ ደረጃ ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡

በቻናል አንድ ፕሮግራሞች በተለይ በዋን ዋሽ ፕሮግራም የሚመጣ በጀትን በአግባቡ አለመጠቀም ችግር የመጣው በጀቱን እንደመንግሥት መደበኛ በጀት አለማየትና የዕርዳታ ገንዘብ በመሆኑ ሆን ብሎ ትኩረት መንፈግ ነው ካሉ በኋላ በእነዚህ ፕሮግራም አፈጻጸም ላይ ጎልቶ የሚታየው ችግር የጥሬ ገንዘብ አስተዳደርና የግንባታ ጥራት ጉድለት ናቸው ብለዋል፡፡

ከዚህም የተነሳ አንዳንድ የሚሠሩ የውኃ ተቋማት ከስድስት ወራትና ከአንድ ዓመት ያልዘለለ አገልግሎት በመስጠት ሥራ ማቆማቸው ዋነኛ መገለጫቸው ነው ብለዋል፡፡ ስለሆነም በሴክተሩ የተለያዩ የአስተዳደር እርከን የሚገኙ የልማት ዕቅድና ኢኮኖሚ አስተዳደር አና የሥነ ምግባር መከታተያ ኦፊሰሮችን በማቀናጀት የጋራ የፕሮጀክት ክትትል ግምገማና ቁጥጥር ማድረግ ችግሮች ሲከሰቱ ወዲያውኑ የመፍታት ሥራ መሥራት የ2010 በጀት ዓመት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የቻናል አንድ ፕሮግራሞች አስተባባሪ አቶ ታረቀኝ ኑራሞ ባቀረቡት ጽሑፍ ከውጭ መንግሥታት ጋር በተደረገ ስምምነት በክልሉ ቻናል አንድ ፕሮግራም ሥር 12 ልዩ ልዩ ፕሮግራሞች የሚካሄዱ መሆኑን ገልጸው በዓመት ከ3.5 እስከ 4.2 ቢሊዮን ብር በጀት የሚመደብ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

One WaSHሆኖም በጀትን በአግባቡ ለታለመለት ዓላማ ባለማዋልና ዝቅተኛ አጠቃቀም በማስመዝገብ የሚከሰቱ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ እነዚህም በጀትን በወቅቱና በተሟላ ሁኔታ ተግባር ላይ ባለማዋልና ባለማወራረድ ምክንያት የገንዘብ ፍሰት መዘግየት ይከተላል፣ በኘሮግራሞቹ የሚረዱ ወይም የሚጠቀሙ ዜጎች ይጎዳሉ፣ በውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖራል፣ የአገልግሎትና የልማት ስራዎች ይጓተታሉ፣ የልማት አጋሮች በፋይናንስ አስተዳደሩ ላይ እምነት ያጣሉ ወደፊትም ሊመጡ የሚችሉ የልማት አጋሮች ፍላጎት ይቀንሳሉ፣ እንዲሁም ለኘሮግራሞቹ ወጪ የሆነ ገንዘብ ደጋፊ ማስረጃ ካልቀረበለት የተሰብሳቢና የተከፋይ ገንዘብ ከ block grant (ከወጪ መርጃ) ስለሚቀነስ ልማት ይጎዳል ብለዋል፡፡

በሥልጠናው ላይ በቻናል አንድ ፕሮግራሞች ምንነትና የበጀት አጠቃቀም፣ በዋን ዋሽ ፕሮግራም እንቅስቃሴ፣ በመንግሥት ፋይናንስ የሕግ ማዕቀፎችና በመንግሥት ግዥ አፈጻጸምና በአፈጻጸም ወቅት በተከሰቱ ችግሮች ዙሪያ ጽሑፎች ቀርበው በውይይት እንዲዳብሩ ተደርጓል፡፡