ሐሰተኛ የመልካም ሥራ አፈጻጸም ማስረጃ ባቀረቡ ሁለት ድርጅቶች ላይ የክልሉ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሚፈጽሙት ማንኛውም ግዥ እንዳይሳተፉ ለሁለት ዓመታት ታገዱ

በጨረታ ሂደት ከሌሎች ተወዳደሪዎች በተሻለ መልካም አፈጻጸም ያላቸው አስመስለው የሐሰት ማስረጃ ባቀረቡ ሁለት ድርጅቶች ላይ የሁለት ዓመታት ዕገዳ የተጣለባቸው መሆኑን በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

ኤጀንሲው ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጠው ዝርዝር ማብራሪያ “አዲሱ የሸዋወርቅ ጠቅላላ የውሃ ነክ ሥራ ተቋራጭ” የክልሉ የመስኖ ግንባታና ተቋማት አስተዳደር ኤጀንሲ ባወጣው ጨረታ ላይ ተሳትፎ ጨረታውን በቀላሉ ለማሸነፍ እንዲረዳው በማሰብ ሐሰተኛ የመልካም ሥራ አፈጻጸም ማስረጃ በማቅረቡ ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በዚህም መሠረት በፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ተቋራጩን የክልሉ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሚፈጽሙት ማንኛውም ግዥ እንዳይሳተፍ የሁለት ዓመታት ዕገዳ አስተላልፎበታል፡፡

በተያያዘ ዜና “አማረ ፋንታሁን ተቋራጭ” የተባለ ድርጅትም በተመሳሳይ ሁኔታ በዚህ ጨረታ ላይ የሐሰት የመልካም ሥራ አፈጻጸም ማስረጃ በማቅረብ የጨረታ ሂደቱን ለማሳሳት በመሞከሩ የክልሉ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሚፈጽሙት ማንኛውም ግዥ እንዳይሳተፍ የሁለት ዓመታት ዕገዳ ተጥሎበታል፡፡በሁለቱም ተቋራጭ ድርጅቶች የተላለፈው ዕገዳ ከታህሣሥ 2 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ የሚታሰብ ሲሆን በየደረጃው ያሉ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ይህንኑ ውሳኔ ተፈጻሚ እንዲያደርጉ ማሳሰቢያው ተላልፏል፡፡