የሥነምግባር ኦፊሰሮች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የክልሉ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አሳሰበ

ethics

በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግሥት የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሥነ ምግባር መከታተያ ኦፊሰሮች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ አሳሰበ፡፡ ኮሚሽኑ ይህንን ያሳሰበው በሀላባ ቁሊቶ ከተማ ሤራ አዳራሽ ከልዩ ወረዳዎችና ዞኖች ለተውጣጡ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ሴክተር የሥነ ምግባር መከታተያ ኦፊሰሮችና የልማት ዕቅድና ኢኮኖሚ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ባለሙያዎች በተዘጋጀው ሥልጠና ላይ ነው፡፡

አቶ ስጦታው ወንጫኖ በክልሉ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነርና በአውታሮች ማስተባበር እና የትምህርትና ሥልጠና ዋና የሥራ ሂደት ባለቤት በሥልጠናው ላይ ተገኝተው ባሰተላለፉት መልዕክት ክልሉ ከሌሎች ክልሎች የተሻለ የሥነ ምግባር መከታተያ መዋቅር የተዘረጋለት መሆኑን አስታውሰው በተቃራኒው የጥሬ ገንዘብ ጉድለት በብዛት መታየት፣ የልማት ፕሮጀክቶች እንቅስቃሴ መጓተትና የበጀት አስተዳደር ችግር መንሰራፋት ራሱ የሥነ ምግባር ኦፊሰሩ ባለበት ሁኔታ ውስጥ መሆኑን ያለንበትን ውስብስብ ችግር ያሳያል ብለዋል፡፡

ምክትል ኮሚሽነሩ አያይዘውም አንዳንድ የሥነ ምግባር ኦፊሰሮች ሙስናና ብልሹ አሠራርን ከመታገል ይልቅ ራሳቸው የሥነ ምግባር ጉድለት ባለባቸው አመራሮች ተፅዕኖ ሥር ወድቀው ችግሩ ሲባባስ አይቶ እንዳላየ መሆናቸው ታሪካዊ ስህተት ሠርተው ታሪካዊ ተወቃሽ ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡

አቶ ስጦታው የሥነ ምግባር ኦፊሰሮችን በሚያነቃቃው በዚህ ንግግራቸው ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትን እንድንታገል የሚያደርጉን አራት አስገዳጅ ሁኔታዎች አሉ ብለዋል፡፡ እነዚህም አንደኛው ፖለቲካዊ ምክንያት ሲሆን ሙስናና ብልሹ አሠራር የሥርዓቱ አደጋ በመሆኑና በመንግሥትም በድርጅትም ሙስናን ለመዋጋት ቁርጠኛ አቋም መያዙ ሲሆን ሞጋች ሕብረተሰብም በመፈጠሩ በሙስና ላይ የሚኖር ድርድር አይኖርም ብለዋል፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ሕጋዊ ሲሆን ሙስናና ብልሹ አሠራር እንዲከላከል እንጂ የሚፈቅድ ሕግ ስለሌላ ሕጋዊነትን ማስፈን መሠረታዊ ግዴታችን ነው ብለዋል፡፡ ስለዚህ ሕግን ለማሰጠበቅ ሁላችንም መሥራት ይኖርብናል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡ ሦስተኛው ተቋማዊ ሲሆን ማናቸውም የመንግሥት አስፈጻሚ ተቋም ወይም መሥሪያ ቤት የተቋቋመው የሕዝብና የመንግሥትን ጥቅም ለማስጠበቅ እስከሆነ ድረስ ሁላችንም ኃላፊነታችንን በመወጣት በየተቋማችን ከሙስናና ከኪራይ ሰብሳቢነት የፀዳ አገልግሎት በመስጠት ልንታገል ይገባል ብለዋል፡፡ አራተኛው ምክንያት ሞራላዊ ሲሆን ማንኛውም ሙሉ ስብዕና ያለው ዜጋ ራሱን ከሙስናና ከብልሹ አሠራር መጠበቅ ያለበት ከመሆኑም በላይ ለሙስና ተብሎ የተፈጠረ ሰው እስከሌለ ድረስ በራሱ ላይ ሊደረግ የማይገባ ክፉ ነገር በሌላው ላይ ላለማድረግ፣ በፈጣሪው ዘንድ ኃጢአት በምድርም ወንጀልን ላለመሥራት ሞራላዊ ኃላፊነት አለበት በማለት አስገንዝበዋል፡፡

ethicsበመሆኑም የሥነ ምግባር ኦፊሰሮች በሕዝብ ውግንና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ቀዳሚ ሚና መጫወት ያለባቸው ሲሆን ውድ የሆነው የሰው ሀብታችን በሙስናና በኪራይ ሰብሳቢነት ምክንያት እንዳናጣ በመከላከሉ ሂደት ውጤታማ ሥራ ልንሠራ ይገባል ብለዋል፡፡ በክልሉ በሚካሄዱ የልማት ፕሮጀክቶች ክትትልና የበጀት አጠቃቀምም ከፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ጋር በመቀናጀት ኮሚሽኑ አስፈላጊውን ደርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ባዘጋጀው በዚህ ሥልጠና ላይ የፋይናንስ አስተዳደር የሕግ ማዕቀፎች፣ በግዥ አፈጻጸም ወቅት የሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎች፣ የቻናል አንድ ፕሮግራሞች ምንነትና እንቅስቃሴ የሚመለከቱ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡