የሰገን አካባቢ ሕዝቦች ዞን ላወጣው የመኪና መለዋወጫ ግዥ ጨረታ ውል ከገባ በኋላ ግዴታውን ያልተወጣው ድርጅት የክልሉ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሚፈጽሙት ማንኛውም ግዥ ላይ እንዳይሳተፍ ዕገዳ ተጣለበት

“ሕይወት ሞላ ጌታ የመኪና መለዋወጫ ድርጅት” ጨረታ አሸንፎ ውል ከፈረመ በኋላ ከሰገን አካባቢ ሕዝቦች ዞን ጋር በገባው ውል መሠረት መለዋወጫዎቹን ባለማቅረቡ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ መለዋወጫ ድርጅቱ የክልሉ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሚፈጽሙት ማንኛውም ግዥ ላይ እንዳይሳተፍ ዕገዳ የጣለበት መሆኑን አስታወቀ፡፡

ኤጀንሲው ይህንን ያስታወቀው የሰገን አካባቢ ሕዝቦች ዞን የመለዋወጫ ግዥ ሂደትን ጠቅሶ ድርጅቱ ግዴታውን ባለመወጣቱ ዕገዳው የተጣለበት መሆኑን ለፌዴራል ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በጻፈው ደብዳቤ ነው፡፡

በመሆኑም በክልሉ መንግሥት የግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅና የአፈጻጸም መመሪያ በሚያዘው መሠረት “ሕይወት ሞላ ጌታ የመኪና መለዋወጫ ድርጅት” ከጥቅምት 17 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በሚታሰብ ለስድስት ወራት የክልሉ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሚፈጽሙት ማንኛውም ግዥ ላይ እንዳይሳተፍ ታግዷል፡፡