በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘና በመረጃ ስፋትና ጥራት ላይ ያተኮረ አትላስ በማዘጋጀት ላይ መሆኑን የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ አስታወቀ

በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግሥት የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ከምንጊዜውም በተሻለ የመረጃ ሽፋን፣ ጥራትና ወቅታዊነት ላይ የተመሠረተ አትላስ በማዘጋጀት ላይ መሆኑን ያስታወቀው ለቢሮው ማኔጅመንትና ከፍተኛ ባለሙያዎች ባዘጋጀው መድረክ ነው፡፡

አቶ ታምራት ዲላ የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ መድረኩን ሲመሩ እንደገለጹት የክልሉን የረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ የልማት አቅጣጫ የሚያመላክትና ለውሳኔ አሰጣጥ አመቺ የሆነ ገላጭና ተአማኒነት ያለው መረጃን ያቀፈ አትላስ መዘጋጀቱ እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ ኃላፊው አያይዘውም በየጊዜው እያደገ የመጣውን የመረጃ ፍላጎት ለማሟላት አስፈላጊው ጥረት መደረግ እንዳለበት አሳስበው መረጃን በአንድ እና ሁለት ዓመት ሳይዘገይ አሁን ያለው ወቅታዊ መረጃን በተጠየቀ ፍጥነት የማቅረብ የብቃት ደረጃ ላይ ለማድረስ ቢሮው የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የአትላሱን የመጀመሪያ ረቂቅ የገመገመው መድረክ ዝግጅቱ ያለፈባቸውን ምዕራፎች ገለጻ ያዳመጠ ሲሆን ከባለሙያዎች በቀረበው ማብራሪያ አትላሱ ከምንጊዜውም የተሻለ ይዘትና ጥራት እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡

በዚህም መሠረት መረጃዎች በሳተላይት ኢሜጅ የተደገፉ ሲሆኑ ማናቸውም መረጃዎች መሬት ላይ ያሉና የሚቆጠሩ ሆነው ቀርበዋል ብለዋል፡፡ ለምሣሌ በመረጃ የተጠቀሱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት እንዲሁም የመሠረተ ልማት አውታሮች የት የት እንዳሉ በሚያመላክት መልኩ ሰፍረዋል ብለዋል፡፡ የክልሉ የደን ሽፋን 19 በመቶ የደረሰ ሲሆን ይህንንም ከሳተላይት የተገኘው መረጃ የደን ሽፋኑን በመቃኘት ከክልሉ ቆዳ ስፋት ጋር በማነፃፀር ሳይንሳዊ በሆነ ዘዴ የሚያስቀምጥ ነው በማለት ገልጸዋል፡፡

ከኦሮሚያና ትግራይ ክልሎች የልምድ ልውውጥ በማድረግ እና ብሔራዊ የአትላስ ዝግጅት ሂደትን በመቃኘት ስታንዳርዱን የጠበቀ የመረጃ ቅንብር ሥራ ለመሥራት ጥረት መደረጉን የገለጹት ባለሙያዎች በጂ ፒ ኤስ የታገዘ የመረጃ ጥናት፣ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን ካርታዎች፣ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን ያዘጋጀው የገጠር ልማት አትላስ፣ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ መረጃ እና ከኢትዮጵያ ካርታ ሥራ ባለሥልጣን የተገኙ የቶፖግራፊና ሳተላይት ኢሜጀሪ መረጃዎች በግብአትነት ውለዋል ብለዋል፡፡

የአትላስ ዝግጅቱ በዘመናዊነቱም ሆነ በመረጃ ጥራቱ ቀደም ሲል የነበረውን አቀራረብ በማሻሻል አንድ ደረጃ ከፍ የሚያደርገው ሲሆን የክልሉን የልማት ፖቴንሽያል በማሳየት፣ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግር ያሉባቸውን አካባቢዎች በማመላከት፣ ለውሳኔ ሰጪ አካላት፣ ለከፍተኛ ትምህርትና ለምርምር ተቋማት፣ ለኢንቨስተሮች፣ ለአስፈጻሚ አካላትና ለልማት አጋሮች ግልጽና ወቅታዊ መረጃ በማቅረብ ከያዘነው በጀት ዓመት አጋማሽ ጀምሮ አገልግሎት ላይ ለማዋል ዕቅድ መያዙ ተገልጿል፡፡