የውጤት ተኮር ዕቅድ ተግባራዊነት የአፈጻጸም አመራር ሥርዓት የመፈጸም ብቃትን ለማሳደግ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ

BSCየለውጥ መሣሪያ የሆነውን የውጤት ተኮር ዕቅድ በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግና የተወጠኑ ዕቅዶችን ወደ ውጤት መለወጥ፣ የአፈጻጸም አመራር ሥርዓትን  የመፈጸም ብቃት ለማሳደግ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ ።

በክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የልማት ዕቅድ ዝግጅትና ኢኮኖሚ አስተዳደር ደጋፊ የሥራ ሂደት፣ ለዞኖችና ልዩ ወረዳ ልማት ዕቅድ አስተባባሪዎች ባዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቢሮ ኃላፈው አማካሪ አቶ አለማየሁ አይበራ እንዳብራሩት፣ ሴክተሩ በተሀድሶ ወቅት የተለዩ ችግሮችን ትኩረት አድርጎ ወደ ንቅናቄ የገባ እንደመሆኑ ውጤታማነትን ለማስመዝገብ ከዕቅድ ዝግጀት እስከ ትግበራና ምዘና ድረስ ያለውን ሂደት እያንዳንዱ ፈጻሚና አስፈጻሚ በሚገባ ጨብጦ ለመፈጸምና ለማስፈጸም መትጋት አለበት ብለዋል።

አያይዘውም ከዕቅድ የሚጀመረው የዕቅድ ዝግጅት ትግበራው፣ አፈጻጸሙና አመዛዘኑ በራሱ ከስትራቴጅክ ዕቅድ የሚመነጭ በመሆኑ፣ ዕለት በዕለት የሚሠሩ ተግባራት በዕውቀት ላይ በመመሥረት መከናወን ስለሚገባቸው በውጤት ተኮር ዕቅድ ላይ የጠራ ግንዛቤ መጨበጥ አስፈላጊ በመሆኑ ሁሉም ሥልጠናውን በተገቢው መከታተል ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

በተሀድሶው ሂደት በሴክተሩ ተለይተው የወጡ ችግሮችን በለውጥ ሠራዊት ትግበራ ውስጥ በማካተት ውጤት ለማስመዝገብ ሁሉም የሴክተሩ አባል በኃላፊነት መንፈስ እንዲቀሳቀስም ጥሪ አቅርበዋል።

DSC09339ከየካቲት20-22/2009 በይርጋዓለም ፉራ ማሠልጠኛ ተቋም በተካሄደው የውጤት ተኮር ዕቅድ  ስልጠና ላይ እንደተገለጸው፣ የስትራቴጂያዊ ውጤት ተኮር ዕቅድ ዝግጅትን በሚመለከት ፣ ዕቅድ አዘገጃጀት ሂደት ላይ ወጥ የሆነ አረዳድ ያለመኖር፣ የዕቅድ አዘገጃጀት ጥራት ያለው አለመሆን፣ የግቦች፣ መለኪያዎችና ኢላማዎች አለመተሳሰር፣ ግቦችና የግብ ውጤቶች የተናበቡ አለመሆን፣ ዓመታዊ የግቦች ውጤትን ከአምስቱ ዓመት ዕቅድ አንጻር እየገመገሙ የተደረሰበትን ደረጃ አለማወቅ፣ ግቦችን ለማሳካት የሚያስችሉ ግብ ተኮር ተግባራትን በመለየት መርሀ-ግብር አለማዘጋጀት፣ የግለሰብ ዕቅድን ከስራ ሂደት ግቦች ጋር በማስተሳሰር አለማዘጋጀት፣ ለስራ ሂደትና ለፈጻሚው የሚሰጡ ግቦችና ተግባራት የክብደት ነጥቦች ከተቋሙ የክብደት ነጥቦች ጋር የተናበበ አለመሆን፣ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ ሂደቶች ካስኬድ ሲደረግ ተግባራትን እንደ ግብ ማስቀመጥ፣ ለግለሰብ የሚሰጡ ተግባራትን ከስራ ሂደት ግቦች ጋር ትስስሩን በጠበቀ መልኩ አዘጋጅቶ አለመስጠት፣ ስታንዳርዶችን መዝግቦ ክፍተቶችን በማረም ስራ ላይ አለማዋል እና ለባህርይ ምዘና መስፈርቶች ዝርዝር አመልካቾችን በማዘጋጀት አለመመዘን ዋና ዋና ችግሮች መሆናቸው ተብራርቷል።

በስልጠናው ወቅት የውጤት ተኮር ዕቅድ ዝግጅትና ሪፖርት የለውጥ ሠራዊት ግንባታና የተሻሻለው የበጀት አስተዳደር አዋጅ የሚሉ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በቀጣይ በቡታጀራና በአርባ ምንጭ ማዕከላትም ተመሳሳይ ሥልጠና ለመስጠት መታቀዱን ለማወቅ ተችሏል።