የሴክተሩ አመራሮች ለልማት የሚመደበውን በጀት በአግባቡ ሥራ ላይ ለማዋል በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ አስታወቁ

የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የሁሉም ዞኖች፣ ልዩ ወረዳዎችና ወረዳዎች የፋይናንስ ሴክተር ከፍተኛ አመራሮችን ያሳተፈ የንቅናቄ መድረክ ከጥር 17-18/2009 ዓ.ም በተካሄደበት ወቅት ለልማት የሚመደበውን በጀት በአግባቡ ሥራ ላይ ለማዋል በየተሰማሩበት መስክ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ አስታወቁ።የክልሉ የመስተንግዶ በጀት አመዳደብና አጠቃቀም ሁኔታ ሥርዓት ባለው መልኩና ወጥነት ባለው አሠራር ተግባራዊ እንዲደረግ፣ ለማስቻልና የበጀት ብክነትን በመቆጣጠር፣ የክልሉ የሀብት አጠቃቀም ይበልጥ በውጤታማነት እንዲተገበር ለማድረግ ታስቦ በተዘጋጀው መድረክ በመገኘት ንግግር ያደረጉት፣ የክልሉ ፋይናንሰና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ታምራት ዲላ ሲናገሩ፣ በየደረጃው በሚገኙ የአስተዳደር እርከኖች ሊኖር የሚገባው የመስተንግዶ በጀት አመዳደብና አጠቃቀም የቁጥጥር ሥርዓትን በማጠናከር የሚስተዋሉ የአፈፃፀም ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ያለመ መሆን ይገባዋል ብለዋል፡፡
የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የበጀት አስተዳደርና የክፍያ አፈጻጸም ሥርዓት ይበልጥ ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግና፣ በክልሉ ያለውን ውስን ሀብት ከወጪ ፍላጎት ጋር ለማጣጣም የሚያስችል፣ የመስተንግዶ በጀት አመዳደብና አጠቃቀም መመሪያ ከጥር 30/2009 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መደረጉን የገለጸው ቢሮው፣ የሴክተሩ ፈጻሚዎችና አስፈጻሚዎች በጥብቅ ኃላፊነትና ተጠያቂነት መርህ የኪራይ ሰብሳቢነትን አመለካከት በማስወገድ ለተግባራዊነቱ ዘብ መቆም እንደሚገባቸውም ጭምር አሳስበዋል።
በዞኖች፣ ልዩ ወረዳዎችና ወረዳዎች እያንዳንዱ የስራ ሂደት በተናጠል በጀት ይዘው የሚጠቀሙ በመሆኑ ቁጥጥር ለማድረግ አስቸጋሪ ሆኖ በመቆየቱ፣ በጀት የመንግስትን ስራ ለማስፈፀም የሚመደብ መሆኑ እየተዘነጋ፣ ለስራ ሂደቶች የተሰጠ ዓይነት አመለካከት በመያዙ፣ የመስተንግዶ በጀት እንደተቋም ሲደመር ከፍተኛ መጠን ያለው በጀት እንደሆነ በጥናት ተረጋግጧል።
በመሆኑም ቁጠባን መሠረት ያደረገ የሀብት አጠቃቀም እውን ለማድረግ እንዲቻል በመመሪያው ውስጥ በእያንዳንዱ ተቋም ለመስተንግዶ የሚውለው በጀት መጠን እንዲካተት የተደረገ ሲሆን ህዝባዊ የባህልና የቋንቋ ሲምፖዚየሞችን ማካሄድ ሲያስፈልግ፣ በዓሉን አስመልክቶ የሚወጡ የመስተንግዶ ወጪዎች ላይ በየአስተዳደር እርከኑ ለሚገኙ አስፈፃሚ አካላት ወይም ካቢኔ የወጪ ዝርዝሩ ቀርቦ ለሀብት ብክነት ባልተጋለጠ መልኩ ውሳኔ እየተሰጠበት ተፈጻሚ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
በመስተንግዶ በጀት አጠቃቀም ዙሪያ በጥናት ከተለዩ ችግሮች የመስተንግዶ አገልግሎት ሳይካሄድ ደረሰኝ በማቅረብ ክፍያ የሚወራረድበት አሰራር መኖሩ፣ ከፋይናንስ እውቅና ውጪ መስተንግዶ በማካሄድ የክፍያ ደብዳቤ በማቅረብ ሂሳብ የሚወራረድበት አሰራር በአብዛኞቹ የአስተዳደር እርከኖች እየተስተዋለ መሆኑ፣ መሥሪያ ቤቶች ለመስተንግዶ አገልግሎት ጥያቄ የሚልኳቸው ደብዳቤዎች የተሳታፊ ብዛት የማይጠቅሱ መሆናቸው፣ በተጨማሪም የተሳታፊ አቴንዳንስ ያለማቅረብና የግልፀኝነት ችግር ያለባቸው ሲሆን ለብክነትና ለኪራይ ሰብሳቢነት መዳረጉ፣ በየከተሞች ከከተሞች ፕላን ዝግጅት፣ ካዳስተር ጥናት፣ ለULGDP ግምገማ ወዘተ… ጋር ተያይዞ ለሚመጡ ባለሙያዎች የሚደረግ ገደብ የሌለው የአልጋና የመስተንግዶ ክፍያ ወጪ ከፍተኛ ብክነት መፍጠሩ፣ የምክር ቤቶች ስብሰባ ሲካሄድ ጉባኤው ከመካሄዱ ቀደም ብለው ባሉ ቀናት እና ጉባኤው ከተካሄደ በኃላ ሂሳቡ ቶሎ ስለማይወዳደቅ አዘጋጅ ኮሚቴዎች ለብዙ ቀናት መስተንግዶ እየተጠቀሙ መቆየት እና በመንግስት የስራ ሰዓት የሚካሄዱ የካቢኔና የማኔጅመንት ስብሰባዎች ወቅት የሚደረጉ የመስተንግዶ ግብዣዎች በየአስተዳደር እርከኑ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መሆኑ ተጠቃሽ ናቸው።
የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በጥናቱ የተካተቱና ለመልካም አስተዳደር ችግሮች ጉልህ አስተዋጸኦ እያበረከቱ ያሉ የኪራይ ሰብሳቢነት አዝማሚያዎች በጣም አደገኛ በመሆናቸው በተሀድሶው ማግስት ሁሉም በየአስተዳደር እርከኑ ያለን የሥራ ኃላፊዎች በቁጭት ለህዝብ ጥቅም በመሥራት መመሪያውን ሥራ ላይ ለማዋል ንቁ ተሳትፎ እናደርጋለን ብለዋል።leadership mobilization