ከሥነ-ህዝብ ሥራዎች አኳያ ሁለ-ገብ፣ ወሳኝና ቁልፍ በሆኑ ስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊተገበር ይገባል ሲሉ የክልሉ ምክትል ፕሬዚደንት አሳሳሰቡ

የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክትል ፕሬዚዳንትና የፐብሊክ ሠርቪስ ቢሮ ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ ይህንን ያሳሰቡት በየዓመቱ ሐምሌ 4 ቀን የሚከበረውን የዓለም የሥነ ሕዝብ ቀን በሀዲያ ዞን ሆሣዕና ከተማ በዓሉን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ነው፡፡

አቶ መለሰ ዓለሙ አያይዘው እንደገለጹት ከእነዚህ ስትራቴጂክ ጉዳዮች አንዱ እያንዳንዱ ቤተሰብ ከገቢ አቅሙ ጋር የሚመጣጠን ማለትም ለመመገብ፣ ለማስተማር፣ ለማልበስ፣ ለማሳከም…ወዘተ የሚችለውን ያህል የቤተሰብ ቁጥር እንዲኖረው በራሱ ፈቃድ የልጆቹን ቁጥር ወስኖና አቅዶ መውለድ የግድ የሚል ሲሆን ይህ ካልሆነ በቤተሰቡም ሆነ በሀገሪቱ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳርፋል ብለዋል፡፡

አንድ ቤተሰብ ከአቅም ጋር የማይመጣጠን ልጅ ከወለደ በበቂ ሁኔታ መመገብና ማሳከም ስለማይችል የጨቅላ ህፃናትና ከ5 ዓመት በታች ያሉ ህፃናት ሞት መጠን ከፍ እንዲል ያደርጋል፡፡ እናትም በአመጋገብ ጉድለት ጤንነትዋ ስለማይስተካከል ያለ ዕድሜዋ የመሞትና በህመም የመሰቃየት ሁኔታ ያጋጥማታል፣ ከሞት የተረፉ ህፃናትም ቢሆኑ በምግብ እጥረት እጅግ የተጐዱ ስለሚሆኑ በዚሁ ሳቢያ የቀጨጩ ልጆች ስለሚበዙ ቢያድጉ እንኳን የትምህርት አቀባበል ደረጃቸው በጣም ዝቅ ያለና ለወደፊቱ ለሀገሪቱ ጐላ ያለ አስተዋጽኦ ማበርከት የማይችሉ ዜጐች እንዲበዙ ምክንያት ይሆናል፡፡ ስለዚህ ልጆችን አቅዶና መጥኖ መውለድ እንደነዚህ ዓይነት ችግሮችን ለመቅረፍ አይነተኛ መንገድ ነው በማለት አብራተዋል፡፡

እናቶች ብዙ ህፃናትን ለመውለድ ሙሉ ዕድሜያቸውን ከሰጡ፣ ለመማር እንዲሁም በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ለመሣተፍ ጊዜ ስለማይኖራቸው፣ ለክልሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት የሚያደርጉት አስተዋጽኦም የዚያኑ ያህል ዝቅ ያለና ያነሰ ይሆናል ካሉ በኋላ ይህም በክልሉ ልማት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚኖረው ሲሆን በተጨማሪም የሴቶች እኩልነትና ተጠቃሚነት ጐልቶ ሊወጣ የሚችለው ሴቶች ጊዜ ኖሯቸው ሲማሩና በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ሲሳተፉ ብቻ ነው በማለት አስገንዝበዋል፡፡

አቶ መለሰ በተጨማሪም የቤተሰብን ቁጥር በዕቅድ የመወሰን ጉዳይ ሴቶችንም ሆነ የክልሉን ህብረተሰብ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዋነኛው መንገድ መሆኑን በመገንዘብ ሁላችንም በተሰለፍንበት የሥራ መስክ የሚፈለግብንን ድርሻ ልንወጣ ይገባናል ያሉ ሲሆን ሀገራዊ የሥነ-ህዝብ ፖሊሲ ከወጣበት ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ የክልላችን መንግሥት የፖሊሲውን አፈጻጸም ከማስተባበርና ከመተግበር አንፃር ግንባር ቀደም ሆኖ መቆየቱ የክልላችንን ህዝብ የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ካለን ፅኑ ዓላማ ጋር የተያያዘ መሆኑን ልንገነዘብና በተለያዩ ሴክተሮች ውስጥ ተካትተው የሚሠሩትን የሥነ-ህዝብ ሥራዎች የልማት ሥራዎቻችን አካል መሆናቸውን ተረድተን በትኩረት ልንሠራ ይገባናል ብለዋል፡፡

የሥነ-ህዝብ ጉዳይ ማለት አንዳንዶቹ በስህተት እንደሚረዱት የሰውን ቁጥር ብቻ ለመቀነስ ዓላማ አድርጎ የሚንቀሳቀስ ሳይሆን የሰዎች የኑሮ ደረጃ እንዲሻሻል በሁሉም መስኮች በትምህርት፣ በጤና፣ በእርሻ፣ በአከባቢጥበቃ፣ በወጣቶች፣ በሴቶችና ህፃናት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በተዋልዶ ጤና፣ የህፃናትና የእናቶች ሞት እንዲቀንስ ወዘተ… የሚደረግ አጠቃላይ የማህበረሰቡን ኑሮ ለማሻሻል የሚደረግ የተቀናጀ ርብርብና የህዳሴውን ጉዞ ለማፋጠን የሚሠራ በመሆኑ በሁለንተናዊ መልኩ ውጤት ማስመዝገብ ይኖርብናል በማለት ንግግራቸውን አጠቃለዋል፡፡

አቶ ታምራት ዲላ የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ በበኩላቸው በአሉ  ዘንድሮ ሲከበር በዓለም ደረጃ ለ28ኛ፤ በሀገራችን ለ24ኛ እና በክልላችን ደግሞ ለ22ኛ ጊዜ መሆኑን አስታውሰው የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ምክር ቤት ወደዚህ ዉሳኔ እንዲደርስ መነሻ ምክንያት የሆነዉ እ፣ኤ.አ ጁላይ 11.1987 የዓለም ሕዝብ ቁጥር 5 ቢሊዮን ከመሙላቱ ጋር በብዙ ሰዉ አዕምሮ ዉስጥ ግንዛቤ ለመፍጠር ነበር ብለዋል፡፡

ይህ ታላቅ አለም አቀፍ የግንዛቤ መፍጠሪያ ንቅናቄ በአለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት በጥልቅ እንቅልፍ ዉስጥ የወደቀዉን የመላዉን አለም ምልአተ ህዝብ ከእንቅልፍ በመቀስቀስና በማንቃት ይሄን ታላቅ የሥነ ህዝብ ፈተና ለማለፍ በሚደረገዉ ትግል ዉስጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ለማድረግ የታለመ ነዉ ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

አቶ ታምራት ዲላ አያይዘውም የክልላችን ሕዝብ በአመት በአማካይ 2.9 እያደገ በአሁኑ ጊዜ 18.9 ሚሊዮን ደርሷል ካሉ በኋላ ይህ በፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኘው የሕዝብ ቁጥር እድገት መፍትሔ ካልተበጀለት አሁን ያለው የሕዝብ ቁጥር በዓመታት ውስጥ እጥፍ እንደሚሆን ይገመታል ብለዋል፡፡

ይህ ከመሆኑ የተነሣም የአብዛኛው ሕዝባችን ዋነኛ መተዳደሪያ የሆነው የግብርና ሥራ በተለያዩ ሰው ሰራሽ ችግሮች (የመሬት ለምነቱን ማጣት፣ በእርሻ መሬት ጥበት፣ በጐርፍ የላይኛው የአፈር ክፍል መከላት) እና በመሳሰሉት ምርታማነቱ የተፈለገውን ያህል መሆን አልቻለም፡፡ እነዚህንና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የክልሉ የሥነ-ህዝብ ምክር ቤት ከ1985 ዓ.ም የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ በዚህም መሠረት እስካሁን 4 የስነ-ህዝብ ኘሮግራም በማዘጋጀት  በሁሉም መንግስታዊ፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የልማት ዕቅድ ውስጥ የሥነ-ህዝብ ጉዳዮች ተካተው ተግባራዊ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከክልል እስከ ቀበሌ የሚዘልቅ የማህበረሰብ የሥነ-ህዝብ ንቅናቄ መድረክ ለማካሄድ ዝግጅቱ ተጠናቆ ከዚህ ጉባዔ በኋላ ወደ ሥራ ይገባል በማለት አስታውቀዋል፡፡

የቤተሰብ ዕቅድ ሕብረተሰብን ለማብቃትና ለሀገር ልማት በሚል መሪ ቃል በተከበረው በዘንድሮው የዓለም የሥነ-ህዝብ ቀን በዓል ላይ ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን የ4ኛው የሥነ ሕዝብ ፕሮግራም የማኅበረሰብ ንቅናቄ ማቀጣጠያ ሰነድም ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡ በፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የሥነሕዝብና ምጣኔ ሀብት ትንተና ባለሙያ የሆኑት አቶ አብርሃም ነጋ “Multi-sector Approach to Harness the Demographic Dividend” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ አሁን ያለው የሥነ ሕዝብ የዕድሜ መዋቅር በአብዘኛው ወጣቶች ያሉበት በመሆኑ ከዚህ የሥነ ሕዝብ ገጽታ በመነሳት ለወጣቱ የሥራ ዕድል በመፍጠር ሀገሪቱ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ልታስመዘግብ የምትችልበት ብሩህ ዕድል አለ ብለዋል፡፡

አቶ ሰሎሞን በቀለ በቢሮው የሥነ ሕዝብ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር 4ኛውን የሥነ ሕዝብ ፕሮግራም ባስተዋወቁበት ገለፃ የክልሉ ቆዳ ስፋት የሀገሪቱን 10% ብቻ ድርሻ ያለው መሆኑን ጠቅሰው የክልሉ ሕዝብ ብዛት ግን ከሀገሪቱ ሕዝብ 21% ድርሻ አለው ብለዋል፡፡ ከዚህ ሁኔታ ጋር ተያይዞ በክልላችን የምግብ ዋስትና ጉዳይ በቀጣይነት እንዳይሳካ እንቅፋት ሊሆኑ ከሚችሉ ነገሮች መካከል ዋነኛው ከመጠን ያለፈ የገጠሩ ህዝብ ጥግግት መጠን (population density) መሆኑን መገንዘብ ይቻላል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የክልሉ አብዛኛዎቹ ዞኖች በሌሎች ክልሎች ከሚገኙ ዞኖች በሕዝብ ብዛት ጥግግት በእጅጉ የሚልቁ ናቸው ካሉ በኋላ ለምሣሌ የጌዴኦ ዞን በካሬ ኪሎሜትር 844 ሰው የሚኖርበት እንደመሆኑ መጠን የከተሞችንም የሕዝብብ ጥግግት የሚልቅ ነው በማለት አስረድተዋል፡፡ ዳይሬክተሩ አያይዘውም ከህዝብ ብዛት መጨናነቅ የተነሣ በእያንዳንዱ ቤተሰብ ጫንቃ ላይ የወደቀውን ችግር በጥልቀት ተገንዝቦ ለወደፊቱ የባሰ ሰቆቃ ከመምጣቱ በፊት የልማቱን ሥራ እጅግ በላቀ ሁኔታ ማሳደግ ለክልላችን የመኖር ያለመኖር ወይም የህልውና ጉዳይ ነው በማለት በአጽንዖት አብራርተዋል፡፡

በበዓሉ ላይ የክልልሉ ሥነ ሕዝብ ምክር ቤት አባላት የዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎችና የሥነ ሕዝብ ጉዳይ ባለሙያዎች እንዲሁም በሥነ ሕዝብ ጉዳይ ዙሪያ የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡