ቢሮው የግዥ አፈጻጸም መመሪያን በማሻሻል ላይ መሆኑን አስታወቀ

በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ይህንን ያስታወቀው ቀደም ሲል አውጥቶት በሥራ ላይ የነበረውን የግዥ አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 13/2005 በማሻሻል ላይ መሆኑን ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ወላይታ ሶዶ ከተማ ባካሄደው የጋራ ምክክር መድረክ ላይ በገለጸበት ወቅት ነው፡፡

ቢሮው እንደገለጸው መመሪያውን ማሻሻል ያስፈለገበት ምክንያት አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ለግዥ የሚመድቡት በጀት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ እና ከዚህ ጋር ተያይዞ በየደረጃው የሚፈቀዱ የበጀት ጣሪያዎችን ከፍ ማድረግ ማስፈለጉ አንዱ ሲሆን፣ መሥሪያ ቤቶች ለግዥ የሚያውሉትን አስተዳደራዊ ወጪዎችንና ጊዜ መቀነስ ሌላው ነጥብ መሆኑ ተወስቷል፡፡

ከዚህም ሌላ ግዥ ፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ግዥ ለመፈጸም የሚኖራቸውን የግዥ ዘዴ አማራጮችን ለማስፋት፣ የሀገር ውስጥ አቅራቢዎች በመንግሥት ግዥዎች ላይ በመሳተፍ የሚኖራቸውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ፣ በግንባታ ግዥዎች አፈጻጸም ሂደት ለኪራይ ሰብሳቢነት በር የሚከፍቱ የአሠራር ሥርዓቶች ላይ ማሻሻያ በማድረግ ችግሩን በተወሰነ ደረጃ ለመቀነስ፣ ግዥ ፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ግዥ ላይ ከሚያውሉት የገንዘብ መጠን ተመጣጣኝ የጥራት ደረጃ ያለውን ግዥ መፈጸም የሚችሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት፣ ቀደም ሲል ለአፈጻጸም ግልጽ ያልነበሩ የአፈጻጸም ሥርዓቶችን ግልጽ በማድረግ የመሥሪያ ቤቶችን የግዥ ሂደት ለማሳለጥ እና መሥሪያ ቤቶች እንደገና በመደራጀታቸው ወይም መዋቅር በመለወጡ ምክንያት የመጡ የስያሜ ወይም የተግባርና ኃላፊነት ለውጦችን በማሻሻያው በማካተት ለአፈጻጸም ግልጽ ለማድረግ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ማሻሻያ የተደረገባቸው አንቀጾች በርከት ያሉ ሲሆኑ ከእነዚሀ መካከል ለግንባታ ዘርፍ፣ ለዕቃ ግዥ፣ ለምክር አገልግሎት እና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚፈጸም ዓለም አቀፍ ግልጽ ጨረታ ግዥ ለመፈጸም ተደንግጎ የነበረው የገንዘብ ጣሪያን እንደየዘርፉ ከነበረበት መጠን ወደ ሦስት እጥፍ የማሳደግ፣ እንዲሁም በመወዳደሪያ ሃሣብ መጠየቂያ የሚፈጸም ግዥን አስመልክቶ ተደንግጎ የነበረው የገንዘብ ጣሪያ ቀድሞ ከነበረው 300 ሺህ ወደ 900 ሺህ ከፍ የማደረግ ረቂቅ ሃሣብ ቀርቧል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በውስን ጨረታ እና በአካባቢ ማስታወቂያ ለሚፈጸም ግዥ ከዚህ በፊት የነበረው ጣሪያ ማሻሻያ የተደረገበት ሲሆን ጥቃቅን ግዥዎች በቀጥታ ሲገዙ የተቀመጠው ጣሪያም ቅድመ ሁኔታዎች ተቀምጠውለታል፡፡

የጨረታ አከፋፈትና የሂደቱ ሥርዓትም ማስተካከያ የሚደረግበት ሲሆን የጨረታ አሸናፊዎች ውል ስለሚገቡበት ሁኔታም የተሻሻለው ረቂቅ መመሪያ ይደነግጋል፡፡ መመሪያው በተጨማሪም የመንግሥት ግዥ ባለድርሻ አካላት ስለሚኖራቸው ሚናም በዝርዝር አስቀምጧል፡፡

ረቂቅ መመሪያው ሥራ ላይ ሲውል ቀደም ሲል የነበሩ የአሠራር ክፍተቶችን በመድፈን ግዥዎችን በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለመፈጸም የሚያስችል ከመሆኑም በላይ ሥራን ለማከናወን ማነቆ የሚሆኑ ችግሮችንም ያስወግዳል የሚል እምነት አለ፡፡

በመመሪያው ማሻሻያ መድረክ ላይ የዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች የክልሉ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ተወካዮች፣ የክልሉ ምክር ቤት የበጀት ፋይናንስና ኦዲት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የክልሉ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ተወካዮች ተሳትፈውበታል፡፡ መመሪያው በየደረጃው ግብአት ከተሰበሰበ በኋላ ዳብሮና ተስተካክሎ በያዝነው በጀት ዓመት ሥራ ላይ እንደሚውል ይጠበቃል፡፡