በውጭ መንግሥታት የበጀት ድጋፍ ለሚካሄዱ ፕሮግራሞች ተገቢው ትኩረት መሰጠት እንዳለበት የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ አስታወቀ

በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግሥት የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ይህንን ያስታወቀው በውጭ መንግሥታትና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች የበጀት ድጋፍ በክልሉ የሚካሄዱ የቻናል አንድ ፕሮግራሞችን አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት ነው፡፡

ቢሮው በተጨማሪ እንዳስታወቀው በተለያዩ የውጭ መንግሥታትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ድጋፍ በክልሉ የሚካሄዱ ፕሮግራሞች አፈጻጸም ደካማ በመሆኑ በመቶ ሚሊዮኖች ብር የሚቆጠር በጀት ሥራ ላይ ሳይውል ለረጂ ድርጅቶች የሚመለስበት ሁኔታ እንዳለ ገልጿል፡፡

የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ታምራት ዲላ ለሠራተኞችና ሥራ አመራር አባላት በተለይ በተዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ ተገኝተው ባሰሙት የመክፈቻ ንግግር ከተለያዩ መንግሥታትና  ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የውል ስምምነት በመፈራረም እንዲሁም ከመንግሥት ግምጃ ቤትና ከህብረተሰቡ የሚገኘውን ገንዘብ በማቀናጀት በግብርና፣ በውሃ፣ በከተሞች ልማት፣ በትምህርት፣ በመንገድና በሌሎችም የኢኮኖሚ ዘርፎች ፕሮግራሞች ተቀርጸው በመካሄድ ላይ መሆናቸውን  ጠቅሰው አፈጻጸማቸውን ለማሻሻል በሁሉም የሚመለከታቸው አካላት የሚሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

DSC09368የቢሮ ኃላፊው በተጨማሪ እንዳብራሩት በልማታዊ ሴፍቲ ኔት፣ በንጹሕ መጠጥ ውሃ፣ በትምህርት ጥራት ማሻሻያ፣ በመሠረታዊ አገልግሎቶች ማሻሻያ፣ በመንግሥት ፋይናንስ አስተዳደር፣ በከተሞች መሠረተ ልማት ማስፋፊያና በሌሎችም የልማት እንቅሰቃሴዎች የተቀረጹ ፕሮግራሞች የተነደፈውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከማሳካት አንፃር ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው አስታውሰው፣ አፈጻጸማቸውን ለማሳደግ ከቀበሌ እስከ ክልል የሚገኙ ተጠቃሚው ኅብረተሰብ፣ በየሴክተሩ የሚገኙ ፈጻሚ ባለሙያዎች እና አመራሩ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በፕሮግራሞቹ አፈጻጸም ላይ ታይተዋል ተብለው በመድረኩ ከተለዩት ዋና ዋና ችግሮች መካከል በቀዳሚነት እነዚህን ፕሮግራሞች ከመንግሥት መደበኛ ሥራ ጋር አጣምሮ በአንድነት ባለማየት ትኩረት አለመስጠት ሲሆን የየሴክተሩ ቅንጅታዊ ድጋፍና ክትትል አናሳ በመሆኑ ምክንያት የበጀት አጠቃቀም ዝቅተኛነት እና የግንባታ ጥራት መጓደል የሚስተዋሉ ችግሮች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የግዥ አፈጻጸም፣ የመረጃ አያያዝ፣ የሪፖርት ወቅታዊነት በአጠቃላይ የመንግሥት ፋይናንስ አስተዳደሩ በተፈለገው መጠንና ደረጃ ሕግን ተከትሎ አለመፈጸም በፕሮግራሞቹ ውጤታማነት ላይ ጥላ ማጥላቱ በውይይቱ ወቅት ተዳሷል፡፡

መድረኩ የፕሮግራሞቹን ውጤታማነት ለማሳደግ የአመለካከት ለውጥ ማድረግ፣ ሥራዎችን በለውጥ ሠራዊት አደረጃጀት መሠረት መፍታት፣ የየፕሮግራሞቹን ቴክኒክና ስቲሪንግ ኮሚቴዎችን ማንቀሳቀስ፣ ከሚመለከታቸው ሴክተሮች ጋር ተቀናጅቶ መሥራት፣ በተገኙ የኦዲት ግኝቶች ላይ ሕጋዊ የማስተካከያ እርምጃዎችን ማስወሰድ፣ የአዋጅና መመሪያ ክፍተቶችን ፈትሾ ማሻሻል፣ የችግሮች መነሻዎችን አጥንቶ ውጤታማ ድጋፋዊ ክትትልን ማጠናከር፣ ከዕለታዊ የሥራ እንቅስቃሴ ተላቆ ስትራቴጂካዊ ለሆኑ ጉዳዮች ትኩረት መስጠት እንደሚያሻ በቁልፍ መፍትሔነት ስምምነት የተደረሰባቸው ነጥቦች ናቸው፡፡