በተያዘው ዓመት በጀትን ለታለመለት ዓላማ በማዋል የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖር ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ አስታወቀ

የሀብት አስተዳደርና ቁጥጥር ሥርዓቱን የማጠናከር እና በሴክተሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የሚደረገው እንቅስቃሴም ተጠናክሮ ይቀጥላል

የክልሉ ሀብት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል በውጤታማነት ላይ የተመሠረተ የሥራ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡ የቢሮው ኃላፊ አቶ ታምራት ዲላ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ወቅታዊ መግለጫ ላይ እንዳብራሩት ሴክተሩ በበጀት ዓመቱ በጥልቅ ተሀድሶው የተለዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመፍታት ባሻገር የሀብት አስተዳደርና ቁጥጥሩ ሥርዓቱን በማጠናከር በጀትን ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

ለ2010 በጀት ዓመት የካፒታልና መደበኛ ፕሮግራሞች ማስፈጸሚያ 33.6 ቢሊዮን ብር የፀደቀ መሆኑን አስታውሰው፣ በጀቱ ሲደለደል በክልሉ ፈጣን፣ ተከታታይና ፍትሐዊነት ያለው ልማት ለማስመዝገብ ዓላማን መሠረት ያደረገ ነው ብለዋል፡፡ ስለሆነም ድልድሉ ፍትሐዊ እንዲሆን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባወጣው ቀመር መሠረት የተካሄደ ሲሆን ቀመሩ በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት መደረጉን አስረድተዋል፡፡

በዚህም መሠረት በተለይ ከግብርና ዘርፍ ጋር ተያይዞ የሚነሱ የመረጃ ጥራት ችግሮችን ለማስወገድ ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን፣ ከኢትዮጵያ ካርታ ሥራ ድርጅትና ከክልል ሴክተር መሥሪያ ቤቶች የተገኙ መረጃዎችን እርስ በእርስ በማመሳከርና በየደረጃው በማጥራት ትክክለኛ መረጃ ላይ እንዲመሠረት ተደርጓል በማለት ገልጸዋል፡፡

በጀት ድልድሉ ሲካሄድ በመርሆዎች ላይ የተመሠረተ ሲሆን አንደኛው መርህ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 41 ንዑስ አንቀጽ 3 ላይ እንደተቀመጠው ሁሉም የክልሉ ነዋሪዎች በመንግሥት ገንዘብ በሚካሄደው ማህበራዊ አገልግሎት እኩል የመጠቀም መብት አላቸው የሚለውን ሃሣብ ታሳቢ የሚያደርግ ሲሆን እንዲሁም በክልሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 117 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይም መንግሥት የክልሉን ነዋሪዎች የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ለማሻሻል እኩል ዕድል እንዲኖራቸው ለማድረግ ሀብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የሚከፋፈልበት ሁኔታ ማመቻቸት አለበት የሚለውን መሠረታዊ መርህ ታሳቢ ተደርጓል፡፡ በመሆኑም በክልሉ የሚኖረው ማንኛውም ነዋሪ በመጠንም ሆነ በጥራት ተመጣጣኝ የሆነ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት እንዲያገኝ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ እንዲሁም የተጀመሩ ክልላዊ ይዘት ያላቸው ትልልቅ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶችን ታሳቢ ያደረገ ድልድል መካሄዱን አስገንዝበዋል፡፡

በሌላ በኩል ድልድሉ የሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን መሠረት ያደረገና ዘላቂ የልማት ግቦችን ያማከለ ሀገራችን በ2030 ወደ ብልጽግና ልትሸጋገር የምትችልበት አቅጣጫን የተከተለ ድልድል እንዲሆን የተደረገ ሲሆን በ2009 በጀት ዓመት በማክሮ ኢኮኖሚ ማለትም በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት የተመዘገቡ ስኬቶችን በማስቀጠል ላይ ያተኮረ እንዲሆን ትኩረት ተሰጥቷል ሲሉ አብራርተዋል፡፡ ስለሆነም የ2010 በጀት በኢዱስትሪ በተለይም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶ መሥራት እንዲቻል በበጀት ድልድሉ ወቅት ታሳቢ ተደርጎ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡

አቶ ታምራት በተጨማሪ ሲያብራሩ የበጀት ድልድሉ በዋናነት ሁሉንም የክልሉን ሕዝቦች ያካተተ እና የልማት ጥያቄዎችን በዘላቂነት ምላሽ ለመስጠት እና የውስጥ ገቢያችንን ሊያጠናክር የሚያስችል እንዲሆን ታሳቢ ተደርጎ ነው የተካሄደው ካሉ በኋላ ዋናው የልማት አቅም ሕዝብ እንደመሆኑ መጠን የበጀት ድልድሉ ሕዝብን ለማነቃነቅ እንዲውልና በቀዳሚነት በልማቱ ተሳታፊ እንዲሆን ለማድረግ በታሳቢነት ተወስዶ ነው የተካሄደው ብለዋል፡፡

የ2010 በጀት ሌላው ትኩረት በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ በኢኮኖሚ ውስጥ የመዋቅር ሽግግር ለማድረግ የመሪነት ሚናውን መጫወት ያለበት ኢንዱስትሪ ከኢንዱስትሪም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንደመሆኑ መጠን ከዘላቂ የልማት ግቦች 1.4 ቢሊዮን ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲውል አድርገናል፡፡ በዚህ በጀት የይርጋለም አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመገንባት ከዚህ ጋር ተያይዞ የገጠር የለውጥ ማዕከላት ይገነባሉ፡፡ አርሶ አደሩ ምርታማነቱን አሳድጎ በአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተጠቃሚ ሊሆን የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ሥራ ይሠራል፡፡ እንዲሁም በተመረጡ አካባቢዎች የመለስተኛ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለመገንባት የአዋጭነት ጥናትና ዲዛይን ሥራ ይሠራል ብለዋል፡፡

ለ2010 በጀት ምንጭ ናቸው ተብለው ከተለዩት አንዱ የክልሉ መደበኛ ገቢ መሆኑን ጠቅሰው ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት 7 ቢሊዮን ብር ይሰበሰባል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ይህም ካለፈው በጀት ዓመት የ17 በመቶ ጭማሪ በማሳየት የበጀቱን 20.8 በመቶ ድርሻ ያለው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ እንዲሁም ከመሥሪያ ቤቶች ከሚሰጡት አገልግሎትና የምርት ሽያጭ 60 ሚሊዮን፣ ከጤና ተቋማት 401 ሚሊዮን፣ ከትምህርት ተቋማት የውስጥ ገቢ 245 ሚሊዮን እና ከማዘጋጃ ቤቶች 1.23 ቢሊዮን ብር የሚሰበሰብ ሲሆን ከጤና፣ ከትምህርትና ከማዘጋጃ ቤቶች የሚሰበሰበው ገቢ ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ10 በመቶ፣ የ22 በመቶ እና የ23 በመቶ ዕድገት ከማሳየቱም በላይ በእነዚህ ዘርፎች የተገኘው ገቢ የሕብረተሰባችን ተሳትፎ እንደጨመረና ሕዝቡ የልማቱ ዋነኛ አቅም መሆኑን ያሳየ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ታምራት በመጨረሻም በ2010 በጀት ዓመት ሰፋ ያለ የልማት እንቅስቃሴ የሚደረግ በመሆኑ ለአፈጻጸሙ ስኬት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አስታውሰው ሴክተሩ የተደለደለው በጀት ለታለመለት ዓላማ በአግባቡ እንዲውል የኦዲት ተደራሽነትን በማሳደግ የተጠናከረ የቁጥጥር ሥርዓት እንደሚዘረጋ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም ቀደም ሲል በተከሰቱ የሀብት ጉድለቶች ዙሪያ ከክልሉ አስመላሽ ግብረ ኃይል ጋር በመሆን የሀብት ማስመለስና ጉድለቶችን ባስከተሉ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ የማስወሰድ ሥራ ይሠራል ብለዋል፡፡ በ2009 በጀት ዓመት በጥልቅ ተሀድሶ ወቅት የተለዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችንም ለመፍታት ሴክተሩ ትኩረት ሰጥቶ ያስፈጽማል በማለት ገልጸዋል፡፡