ሴቶች የተሟላ ነፃነትን ለመቀዳጀት ቁጠባን ባህል አድርገው ከኢኮኖሚ ጥገኝነት መላቀቅ እንዳለባቸው ተገለጸ

ይህ የተገለጸው የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሠራተኞችና ማኔጅመንት አባላት ዘንድሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ41ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ባከበሩበት ወቅት ነው፡፡“የሴቶችን የቁጠባ ባህል ማሳደግ ለህዳሴያችን መሠረት ነው” በሚል መሪ ቃል በተከበረው በዚህ በዓል ላይ ተገኝተው    የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አቶ ዓለማየሁ አይበራ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አማካሪ ባስተላለፉት መልዕክት በሕገ መንግሥታችን ለሴቶች እኩልነት ዕውቅና  ሲሰጥ ከሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች በመነሳት ሲሆን ዴሞክራሲን አሰፍናለሁ፤ ልማትን አፋጥናለሁ የሚል መንግሥት ወይም ድርጅት የህብረተሰቡን 51 በመቶ የሚሆኑትን ሴቶች መብት ካላረጋገጠና ካለሳተፈ ሠላምና ዴሞክራሲ እውን ሊሆን ስለማይችል እና ሴቶችን በልማት ማሳተፍ ብቻ ሳይሆን ተጠቃሚነታቸውንም ጭምር ማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ሴቶች ለመብታቸው ከመታገል በተጨማሪ ቁጠባን ባህል በማድረግ ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ለመላቀቅ ተሳትፏቸውን ማጉላት አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በዕለቱ የሴቶች ዓለማቀፋዊ የትግል ታሪክና ኢትዮጵያ የሴቶችን እኩልነት ከማረጋገጥ አንፃር ተግባራዊ ያደረገቻቸውን የፖሊሲ ውሳኔዎችን የሚመለከቱ ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን የበዓሉን መሠረታዊ ተልዕኮን የሚመለከቱ ጽንሰ ሃሣቦች በጥያቄና መልስ ውድድር በማዳበር ጭምር  ታስቦ ውሏል፡፡march 8